የደብረ ማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከሆቴል ባለቤቶች ጋር የጋራ ውይይት መድረክ አካሄደ።
ደብረ ማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር በሆቴል ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለመፍታትና በዘርፉ የሚሰሩ ሰራተኞችን በካምፓኒ ውስጥ ስልጠና (In-Company Training) በመስጠት የሙያ ብቃታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ውይይት መድረክ ጥቅምት 18 ቀን 2019 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል።
መድረኩን የከፈቱት የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አበበው ግዛቸው ሲሆኑ፣ በንግግራቸው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የከተማው ኢኮኖሚ ዋነኛ አካል በመሆኑ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ለአገልግሎት ጥራት ማሻሻልና ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት የደብረ ማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያለውን የስልጠና አቅም፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሰጡ የመደበኛና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች፣ በሥራ ቦታ የሚሰጥ የካምፓኒ ውስጥ ስልጠና፣ እንዲሁም የሙያ ብቃት ምዘና አገልግሎቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል።
የሆቴል ባለቤቶችም በዘርፉ ያሉ የሰው ኃይል ፍላጎቶችን፣ የሥራ ክህሎት ክፍተቶችን እና በቀጣይ ከኮሌጁ ጋር በስልጠና፣ በሙያ ብቃት ምዘናና በትብብር ሊሰሩባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አቅርበው ገንቢ ውይይት አድርገዋል።
በመጨረሻም በሆቴል ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦትን ለማጠናከር፣ የካምፓኒ ውስጥ ስልጠናዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማካሄድ፣ የሙያ ብቃት ምዘናን በስፋት ለማከናወንና በቀጣይም በተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።